አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ለህዝቡ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች መመለስ የሚያስችለውን ሁለንተናዊ የአደረጃጀት ለውጦች ይዞ ይመጣል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ፡፡
ዶክተር አብርሃም መጪውን የአዲስ መንግሥት ምስረታ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ግልጽ፣ ታማኝ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ አገሪቷን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚመራ መንግሥት መምረጣቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህ የመራጩን ከፍተኛ አደራ ይዞ ወደ ሥልጣን የሚመጣው መንግሥት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአደረጃጀት፣ የአመራርና የአሠራር ለውጦች አድርጎ ይመጣል ብለዋል፡፡
በአዲሱ የመንግሥት ምስረታ በተለይ የብልጽግና ሂደቱን በዕውቀት፣ በክህሎትና በልምድ ሊመሩ የሚችሉና ብቃት ያላቸው አመራሮች የሚመጡበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር አብርሃም ገለጻ ከሚመጡት አዳዲስ ነገሮች በተጨማሪ በለውጥ አመራሩ የተጀመሩ ሂደቶች በልዩ ትኩረት ወደ ፊት ይጓዛሉ፡፡
በተለይም በአሥር ዓመቱ ሊተገበሩ የታቀዱት የኢኮኖሚ የለውጥ ግቦች በጠንካራ መሰረት ላይ ሆነው እንደሚተገበሩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሂደት ሕዝቡም ከምንጊዜውም በላይ ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል ያሉት ዶክተር አብርሃም፥ አቅማችንን አዳብረን ይህን ጊዜ በጋራ ማለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
“አሁን ለመንግስት ብቻ የሚተው አጀንዳ የለም” ያሉት ሚኒስትሩ፥ ችግሮችን በተለይ አሁን የመጣውን የውጭ ጫና በጋራ ሆነን በድል አድራጊነት መወጣት ይጠበቅበናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በነቃ ተሳትፏቸው ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአብላጫ ድምጽ የተመረጠው የብልጽግና ፓርቲም በመጪው መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የመንግሥት ምስረታ ያካሂዳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!