አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው እናት ኮሌጅ በክረምት በጎ አድራጎት ስራ ለአረጋውያን ያስገነባቸውን ቤቶች ለባለቤቶቹ ማስረከብ ጀመረ።
ኮሌጁ በሻሸመኔ ከተማ ለሦሰት እናቶች ያስገነባቸውን ቤቶች ነው ለባለቤቱቹ እናቶች ከነ ቁልፉ ያስረከበው።
ኮሌጁ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች 9 የአረጋውያን ቤቶችን ሲያስገነባ እንደቆየ የኮሌጁ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ገብሬ ተናግረዋል።
በክረምት በጎ አድራጎት ስራ ለቤቶቹ ግንባታ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸዉን አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራው በክረምት ብቻ እንደማይገደብና ቀጣይነት አንዳለው ነዉ አቶ ዘላለም ያስታወቁት።
የአረጋውያን ቤቶች ግንባታሥራዎችን ለማስቀጠል የሚስችል የገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል ”ፅናት” የሚል መጽሐፍ ጽፈዉ ገበያ ላይ እንዳዋሉም ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሁሉም ግንባሮች ብርቱ ፍልሚያ እያደረጉ የሚገኙ የሀገር መከላከያ አባላት ልጆች በኮሌጁ እና በአካዳሚያቸው በነፃ ለማስተማር መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በቤቶቹ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙትና ለእናቶች የመኖሪያ ቤት ቁልፉን የሰጡት የሻሸመኔ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ከድር ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ወራት 18 አዳዲስ ቤቶችን አስገንብቶ ለአቅመ ደካሞች ማስረከቡን ተናግረዋል።
40 ቤቶች ደግሞ እድሳት ተደርጎላቸው ለባለቤቶቹ ተሰጥተዋል ነዉ ያሉት።
እናት ኮሌጅ በሻሸመኔ ከተማ ለአረጋውያን ላስገነባዉ ቤቶችም ምስጋና አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!