Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ መድረክ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ የህንድ ምክትል የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ቲሩ መርቲ ተናገሩ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ከህንዱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲሩ መርቲ ጋር በሁትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታዋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ እና የህንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ሁሉን አቀፍ እና ጠንካራ መሰረት ያለው ነው።

በሃገራቱ መካከል ያለው የኢንቨስትመንት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የንግድና ቱሪዝም በምሳሌነት የሚጠቀስ እና በየጊዜው እየተጠናከረ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሃገራቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በህንድ አፍረካ ፎረም፣ በተባበሩት መንግስታት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑንም አንስተዋል።

ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እያከናወነች ያለውን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ታደንቃለችም ብለዋል።

ከዚህ በፊት የተካሄዱ የህንድ አፍሪካ ፎረሞች የዚሁ ግንኙነት ማሳያዎች እንደሆኑ ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታዋ፥ በቀጣይ በሚካሄዱ ፎረሞች ላይ የኢትዮጵያ ትብብር ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የህንዱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲሩ ሙርቲ በበኩላቸው ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ከመሆኗ ባለፈ አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ካሉ ሃገራት ተርታ ትመደባለችም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ጉልህ ሚና ህንድ ታደንቃለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version