አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ያስጀመረዉን ቤቶች እድሳት በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች አስረክቧል፡፡
ሙሉ ወጪውን በመሸፈን እድሳቱን ያከናወነው የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ ለሀገር አሰተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎች በመጦሪያ ጊዜአቸው መደገፍ፣ መጥቀም፣ ከጎናችሁ አለን ማለት ተገቢ በመሆኑ ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ይህን ዓይነት በጎ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ ÷ ተቋሙ ለመኖር የማይመች ቤቶችን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ከተሟላ የቤት ዕቃዎች ጋር ለሁለት አቅመ ደካማ ጎረቤታሞች ሰርቶ አስረክቧል ብለዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በክረምት ወቅት በጎ ተግባር ላይ በስፋት በመሳተፍ በአዲስ አበባ የ19 ቤቶችን እድሳት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፈ መሆኑ ተገልፆ÷ በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል የአራት አቅመ ደካሞችን ቤቶች እድሳት መጀመሩና በቅርቡ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡