ቴክ

‘አዎ ዶክተር’ የተባለ የዲጂታል ፕላትፎርም ተመረቀ

By Meseret Awoke

September 23, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ‘አዎ ዶክተር’ የተሰኘ የዲጂታል ፕላትፎርም ተመረቀ፡፡

ፕላትፎርሙ ለሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ የዲጂታል ክፍያንም እንደሚያበረታታ የታመነበት ሲሆን÷ እልባት በሚባል አገር በቀል ኩባንያ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዮት ባዩ እንደገለፁት÷ እንደ ‘አዎ ዶክተር’ ያሉ ፕላትፎርሞች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ላይ የተቀመጡ አላማዎችን ለማሳካት ያስችላሉ፡፡

ቴክኖሎጂው በህክምናው ዘርፍ ተመርቀው ወደ ስራ ላልገቡ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት ነው ፡፡

የእልባት ካምፓኒ ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ራያ እንዳስረዱት ፕላትፎርሙ የጤና ችግሮችን ከማቃለሉም በላይ አዳዲስ የዲጂታል ስራ እድሎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

እስካሁን 500 ያሕል የሕክምና ባለሙያዎች በፕላትፎርሙ ተመዝግበዋል ነዉ የተባለዉ፡፡

አዲስ የህክምና ተመራቂዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ያግዛል የተባለው ቴክኖሎጂው ለህክምና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠትና የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላትንም አብሮ ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይሕንንም ለማሳከት በእልባት እና የሊዝ ፋይናንሲግ ተቋማት መካከል የትብብር ስምምነት ተፈርሟል ፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ተወካይ ኮሚሽኑ መሰል የዲጂታል ፈጠራ የሚያስፋፉ ጥረቶችን እንደሚያበረታታ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!