አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የጉና በጌምድር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአሸባሪውና ወራሪው የህወሓት ቡድን ሙሉ በሙሉ መውደሙን የኮሌጁ ዲን አስታወቁ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎችን በወረራ ይዞ በቆየባቸው ጥቂት ቀናት ንጹሃንን ከመግደል በተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል።
የመገናኛ ብዙሃንና የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ በአሸባሪው ህወሓት ሙሉ ለሙሉ የወደመውን የጉና ቤጌምድር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅን በተመለከቱበት ወቅት ዲኑ አቶ ዘላለም ገሰሰ÷ ኮሌጁ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዘጠኝ የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ያሰለጥን እንደነበር አስታውሰዋል።
“ሒሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የመጣው የህወሓት አሸባሪ ቡድን በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባውን የኮሌጁን ንብረት የቻለውን ዘርፎ በመውሰድ፣ ያልቻለውን ደግሞ በማውደም ኮሌጁን ከጥቅም ውጭ አድርጎታል” ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑ 25 ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽኖችን፣ 40 የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መማሪያ ዘመናዊ ኮምፒውተሮችና ሌሎች የወርክሾፕ መሳሪያዎችን አውድሞና ዘርፎ መሄዱንም አስታውቀዋል።
“የአሸባሪው ቡድን ጭፍን ጥላቻን ለመግለጽ ከቃላት በላይ ነው” ያሉት አቶ ዘላለም÷ የኮሌጁን መገልገያ መሳሪያዎች ከመዝረፍ በተጨማሪ ተቋሙ ፈጥኖ ወደ ስራ እንዳይገባ ከአስተዳደር ህንጻ ጀምሮ አላቂ እቃ ሳይቀር ማውደሙን ጠቅሰዋል።
ኮሌጁ 306 ነባር እና 1ሺህ 200 አጫጭር ስልጠናዎችን የሚከታተሉ ተማሪዎች እንደነበሩት አስታውሰዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ዝርፊያና ውድመት ምክንያት ኮሌጁ ለጉዳት በመዳረጉ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማስተማር የማይችልበት ደረጃ ላይ ነው ያሉት ዲኑ።
ኮሌጁ ወደ ነበረበት ደረጃ ተመልሶ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል መንግስት፣ ህብረተሰቡ እና ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ኮሌጁ ህብረተሰቡ ልጆቹን በቅርበት ለማስተማር ባለው ፍላጎት ገንዘብ አዋጥቶ የገነባው እንደነበር የገለጹት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አወቀ ዘመነ ናቸው።
አሸባሪው ቡድን ለጥቂት ቀናት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የንጹሀንን ህይወት ከማጥፋት ባለፈ ለትውልድ ሊጠቅሙ ይችላሉ ያላቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት አውድሞና ዘርፎ መሄዱን አመልክተዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን በወረራቸው ውስን አካባቢዎች ለቀናት ሲቆይ ካደረሰው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ውድመት በተጨማሪ ከ100 በላይ ንጹሀንን መግደሉን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!