Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የ”ሄር ኢሴ” ባህላዊ ህግ በአለም ቅርስነት ለማስመዘገብ እንቅስቃሴ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)”ሄር ኢሴ” የኢሣ ማህበረሰብ ባህላዊ ያልተጻፈ ህግ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሣይንስና የባህል ድርጅት/ዩኒስኮ/ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ፣የጅቡቲና የሶማሌ ላንድ የኢሣ ማህበረሰብ አባቶች የተሣተፉበት በባህላዊ ህጎች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በድሬደዋ ተካሂዷል።

የሲቲ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ኃላፊ ወይዘሮ አያን አሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ”ሄር ኢሴ” ባህላዊ መተዳደሪያ ህግ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በ16ተኛው ክፍል ዘመን 44 የኢሣ ማህበረሰብ አባላት ተቀምጠው ያጸደቁት ነው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሶማሌ ህዝብ አንድ አካል የሆነው ኢሣ ማህበረሰብ ህጉን ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል እየተቀባበለ እየተመራበት እንደቆየ አስረድተዋል።

ህጉ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድ የሚገኙትን የማህበረሰቡን አባላት ያስተሳሰረ መሆኑን ጠቁመው ÷ባህላዊ ህጉ ኢትዮጵያ ለምትገነባው የዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግብአትነት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በአለም ቅርስት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ አያን፤ ቅርሱ ሲመዘገብና ሲተዋወቅ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን ይበልጥ ያስተሣስራል ነው ያሉት።

የማህበረሰቡን ባህላዊና ታሪካዊ የጋራ እሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቱሪስት መስህብነት በመዋል በጋራ የማደግ ራዕይን እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሚዳሰሱ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ የሚያስችል ሰነድ ዋና አዘጋጅ አቶ ገዛኻኝ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ባህላዊው ህግና ስርዓቱ በትውልድ ቅብብሎሽ እየዳበረ የመጣ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባሀላዊ ህጉ እኩልነትን፣ሰው በሰውነቱ የሚከበርበትና የሚተዳደርበት የመቻቻልና የሰላም እሴቶችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version