የሀገር ውስጥ ዜና

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለብሔራዊ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት 3ሺህ መጻሕፍት አበረከተ

By Meseret Awoke

September 23, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ጅማ ዩቨርሲቲ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በኢዲስ አበባ እየተገነባ ለሚገኘው ብሔራዊ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት 3ሺህ የተለያዩ መፃህፍቶችን ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡

መጻሕፍቱን የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ተረክበዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተኮር የትምህርት ፍልስፍና እንደሚከተል ተናግረው በ2013 ዓ.ም ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ካደረገው 32 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ባሻገር 100ሺህ ችግኞችን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መተከሉን ገልፀዋል፡፡

በአጠቃላይ 211ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ ስራዎችን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተግባራዊ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡

ለብሔራዊ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት የተደረገው የ3ሺህ መጻሕፍት ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ÷ በአዲስ አበባ እየተሰሩ ካሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካካል አንዱ ብሔራዊ የህዝብ ቤተ መንግስት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ አሁን ግንባታው መጠናቀቁ ተናግረው በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት እንደሚመረቅ አስረድተው÷ አጠቃላይ ከ2 ሚሊየን በላይ መፃህፍቶችን መያዝ የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው የመጻሕፍት ድጋፍ ያመሰገኑት ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን÷ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመስገን አለባቸው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!