አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ ወጥ መንገድ የተወረረ ከ6 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬትማስመለሱን የጌዴኦ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው “ከተሞችን በፕላን በመምራት ህገ ወጥ የመሬት ወረራን እንከላከል ” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ የመምሪያው ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ እንዳሉት÷ በዞኑ ውስጥ በከተማ መሬት ህገወጥ ወረራ፣ ግንባታና ሰፈራ ተካሂዷል።
በተጨማሪም የመንግስት ይዞታን ወደ ግል ማዞርና መሰል ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
“መምሪያው በተጠናቀቀው ዓመት ባደረገው ክትትል በዞኑ ከ13ሺህ 500 ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት በህገወጥ መንገድ መወረሩን ለይቷል” ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ከ6ሺህ የሚበልጠውን ወደ መንግስት መሬት ባንክ ተመላሽ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል።
በመሬት ወረራው ዲላ፣ ወናጎና ጨለለቅቱ ከተሞች በቀዳሚነት የጠቀሱት አቶ አብዮት÷ ከመሬት ወረራ በተጓዳኝ 189 ህገወጥ ግንባታዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ፥ የከተማ መሬትን አለአግባብ በማስተዳደር በመንግስትና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሱ 12 የማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎችና ሁለት አመራሮች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው፥ በህገ ወጦች ላይ የተጀመረውን ህጋዊ እርምጃ ከማጠናከሩ በተጓዳኝ የዞኑን ገቢ በማሳደግና በማዘጋጃ ቤቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ከተሞችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በንቅናቄው መድረክ የዞንና ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የማዘጋጀ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።