ስፓርት

አትሌት አባዲ ሃዲስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

By Tibebu Kebede

February 05, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በበርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረው የ22 ዓመቱ ወጣት አትሌት አባዲ ሀዲስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

አትሌት አባዲ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በመከወል በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፏል።

አባዲ ሀዲስ በመቐለ ሃይደር ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቆይቶ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

አትሌት አባዲ ሃዲስ በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ልዩ ስሙ እንዳመሆኒ ወረዳ ጥር 27 ቀን 1990 ዓ.ም የተወለደ ሲሆን፥ የአትሌቲክሰ ህይወቱን በእንዳመሆኒ የአትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ጣቢያ ጀምሯል።

በመቀጠልም በማይጨው አትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብቶ መደበኛ ስልጠናውን ሲያጠናቅቅ ትራንስ ኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ክለብን በመቀላቀል ህይወቱ እስካለፈበት እለት ድረስ ክለቡን፣ ክልሉንና ሃገሩን ሲያስጠራ ነበረ።

በኦሊምፒክ በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሪዮ በተካሄደው የ2016 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በ10 ሺህ ሜትር፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዶካ ኳታር በተካሄደው የ2019 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር እንዲሁም በለንደን በተካሄደው የ2017 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር 7ኛ ደረጃ በማግኘት አጠናቋል።

በተመሳሳይ በ2017 በኡጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር 3ኛ ደረጃ በመያዝ የነሃስ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡

የአትሌት አባዲ ሀዲስ የቀብር ስነ ስርዓት በነገው እለት የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የትግራይ ክልል አትሌቲክሰ ፌዴሬሽንና የክለቡ አመራሮችና ሌሎች ኃላፊዎች በተገኙበት በትውልድ ስፍራው እንደሚከናወን የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን አስታውቋል።