የሀገር ውስጥ ዜና

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚኖሩ ስደተኞች የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል- አቶ ደመቀ መኮንን

By Alemayehu Geremew

September 22, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተመድ ጠላቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን አቶ ደመቀ በኒውዮርክ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ ጋር ተገናኝተው ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም በስደተኞች አያያዝ፣ በድጋፍ አሰጣጥ እና በስደተኞች ካምፕ አስተዳደር ዙሪያ ጠቃሚ ሃሳቦች ተለዋውጠዋል።

“በኢትዮጵያ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ በቅርበት መስራት ይገባል” ሲሉም አቶ ደመቀ አብራርተውላቸዋል፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለሚኖሩ ስደተኞች ድጋፉን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው÷ በቀጣይ የሚያጋጠሙ ችግሮችን ለመሻገር በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ማስገንዘባቸውን ከጽህፈት ቤታቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡