አዲስ አበባ መስከረም 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ምክንያት የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን መውሰድ ለማይችሉ ተማሪዎች ተለዋጭ መርሀ ግብር እንደሚኖር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከአሸባሪው ቡድን ነፃ በወጡ አካባቢዎች የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ ቢጀመርም ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 2፣2014 ዓ.ም ለሚሰጠው የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ በማይችሉ አካባቢዎች መደበኛ የተማሪዎች ፈተና በሌላ መርሀ ግብር እንደሚሸፈን ነው ትምህርት ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫም የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 2፣2014 ዓ.ም እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ከ3 ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡
በወረራው ምክንያት ከወደሙት ትምህርት ቤቶች መካከል ከ2 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው የመልሶ ግንባታው ሂደት ጊዜ የሚወስድ እና የሁሉንም አካል ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዘርፏል፤ ማንቀሳቀስ ያልቻለውንም አውድሟል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አንዳንድ ትምህርት ቤቶችንም የጦር ካምፕ ስላደረጋቸው ጦርነት ተካሂዶባቸዋል ብለዋል፡፡
በሽንፈት ሲሸሽም ጣራ በመንቀል እና ሕንጻ በማፍረስ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ጌታሁን “ፈተናውን መውሰድ ያልቻሉ ተማሪዎች የአካባቢያዊ ሁኔታው ሲመቻች እና በሥነ ልቦና ለፈተና ዝግጁ ሲሆኑ በሌላ መርሀ ግብር እንዲወስዱ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
በየትኛውም መንገድ ተማሪዎቹ የመፈተን አማራጮቻቸው ካልተመቻቹ ሌላ መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ በመደበኛ ተማሪነት ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎችን ሥነ ልቦና በመጠገን፣ የትምህርት ቤቶችን ምገባ በማስጀመር እና የተለያዩ አጋዥ የትምህርት ቁሳቁስ በማበርከት ኢትዮጵያውያን እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ዶክተር ጌታሁን ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!