የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ክልልን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው­- የክልሉ መንግስት

By Tibebu Kebede

February 04, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልልን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የክልሉን የስድስት ወራት  የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፥ በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮችም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በመግለጫው፥ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ከፀጥታ አካላት እንዲሁም ከመላው ህብረተሰብ ጋር ባደረገው ርብርብ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ የተወሰኑ ዞኖች አልፎ አልፎ  የሚታየውን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታትም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንም የህዝቡን የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረውን ሀገራዊና ክልላዊ ለውጦችን አጠናክረን ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነውም” ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት፣ በአቋራጭ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝና የህዝቡን የራስን እድል በራስ የመወሰን ህገ መንግስታዊ መብቶችን ለመንፈግ የሚደረጉ ጥረቶችን በማክሸፍ ረገድ ውጤታማ እንደሆኑም ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ ይህን ተገንዝቦ  ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምን በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር፣ ለውጡን መደገፍ እና ውጤቱንም ለማጣጣም ከመንግስት ጎን ሆኖ መስራት እንደሚገባውም አመልክተዋል።

አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫው አክለውም፥ “በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች በተቀመጡ ዋና ዋና ግቦች ዙሪያ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል” ብለዋል።

በተለይም በግብርና፣ ሥራ እድል ፈጠራ፣ ትምህርት፣ መንገድና የመጠጥ ውሃ እንዲሁም የእናቶችና ህፃናትን ሞት ከማስቀረት አንፃር ተስፋ ሰጪ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በበጀት  ዓመቱ  ከዝግጀት ምዕራፍ ጀምሮ በግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት፣ በመካናይዜሽን መሳሪያዎች፣ በአፈርና ውሃ  ጥበቃ እንዲሁም የማዳበሪያ  አቅርቦት የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን አስረድተዋል።

በዚህም በመኽሩ ወቅት በዋና ዋና ሰብሎች ለማግኘት ከታቀደው 182 ሚሊዮን ኩንታል ወስጥ እስካሁን  ባለው አፈፃፀም ከ85 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ድህነትን ለመቀነስና የሥራ አጥነት ችግር ለመቀነስ በተደረገው ጥረትም የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎችን ጨምሮ  ከ600 ሺህ በላይ  ሴቶችና  ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የቢሮው ኃላፊ እንዳሉት የህዝቡን የልማት  ችግሮችን ለመፍታትም 27 የመንገድ ልማት ፕሮጄክቶችን ለማጠናቀቅ በተደረገው ጥረት  በግማሽ የበጀት  ዓመቱ አፈጻጸሙ  ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል።

ከ496 በላይ የውሃ ፕሮጄክቶች በማጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸው በዚህም ከ290 ሺህ በላይ የገጠር ነዋሪዎች  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ መስተዳድርና  አዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በመተባበር አፋን ኦሮሞ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጥ  እየተደረገ ነው።

በክልሉ ከ9 ሚሊዮን 200ሺህ በላይ ተማሪዎች በመማር ማስተማር ሂደት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት የቢሮው ኃላፊ፤ “ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሙሉ አቅማችን እየሰራን ነው” ብለዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ