አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች የውጭ ዜጎችን ደህንንት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ረዳት ሚኒስትር ቼን ሽያዶንግ ገለፁ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የሆኑትን ቼን ሽያዶንግ በዛሬው እለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይታቸውም ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማስታወስ፤ በአሁኑ ስዓት የሀገራቱ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ታሪካዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ውጤታማ፣ በተግባር የተደገፈ፣ ተገማች እና ስትራቴጂያዊ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሂሩት፥ ይሄው ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ከሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪም በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ስዓት በቻይና የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ቻይና ሙሉ አቅም እና ብቃት እንዳላት ኢትዮጵያ እምነቷ መሆኑንም ሚኒስትር ደኤታዋ ገልጸዋል።
ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደ ወትሮው ሁሉ ከቻይና ጎን በመቆም ወረርሽኙን ለመከላከል አስፈላጊውን ትብብር እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የዓለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገች መሆኗንም ሚኒስትር ደኤታዋ ገልፀዋል።
በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ረዳት ሚኒስትር ቼን ሽያዶንግ በበኩላቸው፥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ በመግለጽ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዥንፒንግ ያስተላለፉትን መልዕክት በማንሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቻይና መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና ብሎም ለመቆጣር ሀገር አቀፍ ስርዓት መዘርጋቱን እና በሽታውን ለመቆጠጣር የሚያስችል ሙሉ አቅምና ቁርጠኝነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቻይና ከዓለም መንግስታት እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመቀራረብ እና በትብብር እየሰራች መሆኑን ያስታወሱት ቼን ሽያዶንግ፥ ቫይረሱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል መፍትሄ በቅርቡ ለማግኘት እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በቻይና የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን እና ኢትዮጵያውያንን ደህንንት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቅዋል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በሚያከብሩበት በዚህ ወቀት ሀገራቱ በትብብር እያከናወኗቸው ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በውጤት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
ሀገራቱ በቻይና አፍሪካ ትብብር፣ በተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ረዳት ሚኒስትር ቼን ገልጸዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!