Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ባሌ ዞን የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክትን በዛሬው እለት መረቁ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ህዝቡ ከዚህ በኋላ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፈል ወጥቶ በልማት ላይ እንዲሰማራ መልእክት አስተላልፈዋል።

ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ዐቢይ፥ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስም በመደማመጥ እና በመረዳዳት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ በዛሬው እለት የተመረቀው የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የአርብቶ አደሮችን ህይወት በመቀየር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በመንግስት እርዳታ ስር የነበሩ ሲሆን፥ ከዚህ በኋላ ግን ራሳቸውን ከመቻልም አልፈው ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም፥ ወረዳው ያለውን የመንገድ ችግር ለመፍታት ከቀጣዩ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጎባ- ነጌሌ ቢታካ መንገድ ግንባታን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በዛሬው እለት የተመረቀውና በምዕራብ ባሌ ዞን በደሎመና ወረዳ የሚገኘው የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክት ከ400 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ተገልጿል።

ከ36 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው መስኖ ልማት ፕሮጀክቱ 1 ሺህ 123 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መሆኑ ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚህ በወልመል ወንዝ ላይ ለሚገነባ ተጨማሪ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በዛሬው እለት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ግንባታው በ3 ቢሊየን ብር ይካሄዳል የተባለው አዲሱ የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 11 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለውም ተገልጿል።

በተመሳሳይ በምስራቅ ባሌ ዞን ራይቱ እና ጊኒር ወረዳዎች መካከል ለሚገነባው የዲኒቅ ቻልቻል የመስኖ ልማት ፕሮጀክትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በ2 ነጥብ 822 ቢሊየን በር የሚካሄድ ሲሆን፥ ገንባታውም በ2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

4 ሺህ 114 ነጥብ 7 ሄክታር መሬትን ያለማል የተባለው የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ፤ በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኙ የራይቱ እና የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ታውቋል።

በሙለታ መንገሻ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version