አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ቡድን ወረራ ሳቢያ ከሰሜን ወሎና ከአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እየቀረበ እንደሚገኝ ብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽነር ገለጹ።
ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከፋና ብድሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የትናንት ምሽት ዜና መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷ ለ346 ሺህ 818 ተፈናቃይ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ እየቀረበ ነው።
በዚህም መሰረት ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ደሴና ኮምቦልቻ ለሚገኙ 118 ሺህ ወገኖች በመንግስት ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን÷ 60 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በአጋር ድርጅቶች በተለይም ኤፍ.ኤች አይ በሚባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል ።
በተጨማሪም ለ 92 ሺህ 318 ሰዎች እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን በሚገኝባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የሚኖሩና ከአካባቢው ለመዉጣት ያልቻሉ አቅመ ደካሞች ፣ ህጻናት የሚያጠቡ እናቶችና አካል ጉዳተኞች አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በአለም ምግብ ፕሮግራም በኩል የምግብ ፣ የመድጋኒት ፣ የመጠጥ ዉሃና ሌሎች አቅረቦቶች በአፋጣኝ እንዲደርሱ ስምምነት ላይ መድረሳቸዉን ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
የአለም አቀፍ ህግን ተከትሎ ስራዉን እንዲያከናዉን ከአለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ስምምነት ላይ በመድረሳቸውም ከመስከረም 5 ቀን 2014 ጀምሮ የእርዳታ አቅርቦቱን ከኮምቦልቻ ማጓጓዝ መጀመሩን አስረድተዋል ።
በሌላ በኩል በሰሜን ወሎ ለሚገኙ 11 ሺህ 500 ለሚሆኑ ዜጎች ፣ በሰሜን ጎንደር ለሚገኙ 119 ሺህ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።
በሰሜን ወሎም ሆነ በአፋር አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ እዚህ ግባ ሚባል አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ÷ የእርዳታ አቅርቦት ስራዉን ለማቀላጠፍና ለማሳለጥ በባህርዳር ፣ በጎንደር ፣ በደሴና በሰመራ የእርዳታ ማስተባበሪያ ማእከላት መቋቋማቸዉን ነው ያስታወቁት ።
የእያካባቢው አስተዳደሮች ፣ የሚመለከታቸው የክልል ሴክተር ቢሮዎችና የፌዴራል ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች የሚገኙባቸው እነዚህ ማእከላት የሰብዓዊ እርዳታው በፍጥነት እና በትክክል ለተረጂዎች እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል ኮሚሽነሩ ።
የአፋር ክልልን በተመለከተ ሁሉም አካባቢዎች ከወራሪው ሃይል ነጻ መዉጣታቸውን አውስተው÷ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ከ76 ሺህ 500 በላይ ተፈናቃዮች እርዳታ እያገኙ ነው ብለዋል ።
ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ በወራሪው ሃይል የወደሙ የጤና፣ የትምህርትና የዉሃ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና የተፈናቀሉ ባለሙያዎችን በመመደብ ተቋማቱ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉም አብራርተዋል ።
የሚገኘውን የእርዳታ አቅርቦት አቀናጅቶ ለተረጂዎች የማድረስ እጥረት እንዳለ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ÷ በተቋቋሙት የአስቸኳይ እርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከላት አማካይነት እርዳታውን በፍጥነትና በትክክል ለተረጂዎች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል ።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በድርቅ በጎርፍ አደጋና በግጭት ምክንያት 11 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎች እርዳታ እንደሚሹም ከኮሚሽነር ምትኩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል ።
በአሰፋ አህመድ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!