Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ሰላም የምትሆንበትና መልካም ነገሮች የሚሰማበት እንዲሆን እንመኛለን-የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ሰላም የሚሰፍንበትና መልካም ነገሮች የሚሰሙበት እንዲሆን ምኞታችን ነው ሲሉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የናይጄሪያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢኖሰንት አሎማ ኢዌጆ፣ በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ፍራንስዋ ዱሞንት፣ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ፣ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ፣ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ እና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፥ “አዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚጠናከርበት ይሆናል” ብለዋል።

“ዓመቱ ኢትዮጵያ ሰላም የምታገኝበትና ብዙ መልካም ነገሮች ጎልተው የሚሰሙበት ይሆናል፤ ይሄም እንደሚመጣ ተስፋ አለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰላም ከምንም በላይ እንደሚያስፈልጋት ተናግረው፤ ዓመቱ ሰላም ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር በመስራት የሁለትዮሽ ትብብሩ ከፍ እንደሚልም አውስተዋል።

በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የሚያደርጓቸው ድጋፎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

“አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ መልክዓ ምድሯ በውብ ቀለማት የምታሸበርቅበት ወርቃማ ጊዜ እንደሆነና ደምቃ የምትታይበት ጊዜም ነው” ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የደስታ፣ የስኬት፣ የብልጽግና እንዲሁም መልካምና ጤናማ ሕይወት የሚኖሩበት ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version