አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ሺህ 562 ድርጅቶች ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮች ተቀላቅለው በመገኘታቸው እንዲሁም የ479 ድርጅቶች ምርቶች ጊዜ ያለፈባቸው በመሆኑ እንዲወገዱ መደረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ተከተል ጌቶ÷ከባለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በተሰሩ የኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ሥራዎችን ጥታቸውንና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ወደ ገበያው በሚያቀርቡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
በተደረገው ክትትል ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች ተቀላቅለውባቸው ከተገኙ ምርቶች መካከል ÷ ቅቤ፣ በርበሬ፣ ወተት፣ አይብ፣ ማር፣ ዱቄት፣ ቡና፣ ዘይት፣ እንጀራ እና የመሳሰሉት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የወንጀል ድርጊቶቹ÷ በርበሬን ከ እርድና ሸክላ አፈር እንዲሁም ከስንደዶ ማቅለሚያ ኬሚካል ጋር በመደባለቅ፣ ማርን ÷ከሞላሰስ ወይም ስኳር ጋር በመደባለቅ፣ ቡናን÷ ከዋንዛ ፍሬ ጋር በመደባለቅ፣ ቅቤን÷ ከሙዝ፣ ከቡላ እና መሰል ነገሮች ጋር ቀላቅሎ በማቅረብ፣ ጤፍን÷ ከካሳቫ፣ አሸዋ እና አፈር ጋር ቀላቅሎ ለገበያ በማቅረብ፣ ዱቄትን÷ ከተበላሽ ዱቄት ጋር በመቀላቀልና በማቅረብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲፈፀሙ የነበሩ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የወንጀል ድርጊቶቹን በመከታተልና ወንጀለኞቹን በመያዝ ረገድ በየደረጃው የተዋቀሩ የንግድ ቢሮዎች ግብረ ሀይል እና ባለድረሻ አካላት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ተጠቁሟል፡፡
እንደነዚህ አይነት ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡
በንግድ ቢሮ ግብረ ሀይል ወይም ከባለድረሻ አካለት ጋር ከሚሰሩ የቁጥጥር ስራዎች በተጨማሪ ሸማች ማህበረሰቡም ጥቆማ በመስጠት ጥቅም ላይ ቢውሉ ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶች እንዲወገዱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡