ጤና

በወሊድ ጊዜ የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመቀነስ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

By Tibebu Kebede

February 03, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

“እናት የቤተሰብና የሀገር ምሰሶ ናት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ በክልሉ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ የጤናማ እናትነት ወር በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

የፓናል ውይይቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች በተገኙበት ነው በጋምቤላ ሆስፒታል የተካሄደው፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፥ በክልሉ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

እናቶች ከቅድመ ወሊድ ጀምረው በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመው፥ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

በዘርፉ ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነት የተጠናከረ ድጋፍ ለመስጠት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

የእናቶችና ህፃናት ጤና አስተባባሪ አቶ ባልቻ በርገኔ በበኩላቸው በክልሉ በጤና ተቋማት የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎት ሽፋን እየተሻሻለ ቢመጣም እንደ ሀገር ሲታይ ብዙ ስራዎችን እንደሚፈልግ አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆን እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር ለዝቅተኛነቱ እንደምክንያት ተጠቅሰዋል፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች በበኩላቸው እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱና አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ በባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

እናቶች ወደ ጤና ተቋም በአመኔታ እንዲመጡ ጥንቃቄና አክብሮት የተሞላበት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ መገለጹን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።