Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ጥምረት ለማስቀጠል 15 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቀንድ አምስት ሀገራት በጋራ የኢኮኖሚ ጉዳዮችና በቀጠናው ሁሉን አቀፍ ትብብር ዙሪያ በጅቡቲ እየተወያዩ ነው።

የአምስቱ ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ሀገራቱ በጋራ የኢኮኖሚ ጉዳዮች በቀጠናው ሁሉን አቀፍ ትብብር በተለይም የንግድ ልውውጡ በሚጠናከርበት እንዲሁም ውጤታማ የሚሆንባቸው መንገዶችን ለማስፋት በሚያስችሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ዙሪያ ነው እየመከሩ የሚገኙት።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በሚል ስያሜ ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው ይህ የጋራ መድረክ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያን ያካተተ ነው።

በቀጠናው ያለው ጠንካራ ፖለቲካዊ ግንኙነት የፈጠረው መልካም አጋጣሚን በመጠቀም በተለይም በጋራና በመቀናጀት የተሰሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጠና ጥምረት ባሉ ተሞክሮዎች ዙሪያም ውይይት እየተካሄደ ሲሆን፥ የቀጠናውን ጥምረት አጠናክሮ ለማስቀጠል 15 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግና እነዚህን የፋይናንስ ግብዓቶች ለሟሟላት በሚያችሉ መንገዶች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በተለይም ካለፈው አመት ወዲህ በትራንስፖርት፣ ኃይልና በዲጂታል ዘርፉ መሰረተ-ልማት ዙሪያ የተፈረሙ ስምምነቶች መሰረት የተጀመሩ ሥራዎች የሚገኙባቸውን ደረጃ በመገምገም አበረታች ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሀገራቱ በጋራ መስራታቸው ለወጣቶች የስራ እድልን ለማስፋፋትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ለማፋጠን እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በግጭት ለዘመናት የተጎዳውን የቀጠናውን ህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚረዳ መገለፁን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version