Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሚኒስቴሩ በሃገር ውስጥ በተለያዩ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ባደረገው ጥረት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ማዳን ቻለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በሃገር ውስጥ በተለያዩ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ጉዳዮች በተደረገ ጥረት በድምሩ እስከ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪን ማዳን መቻሉን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በትራንስፖርት ዘርፉ በተደረገው ጥረት አበረታች መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም 954 ሺህ ቶን ጭነት በታጁራ ወደብ በኩል በመስተናገዱ ለጅቡቲ ወደብ ይወጣ የነበረን 91 ነጥብ 935 ሚሊየን ብር የሎጂስቲክስ ወጪን ማዳን መቻሉን ገልጿል፡፡

ወጪ እቃዎችን በሃገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጎ በመላኩም እስከ 103 ነጥብ 14 ሚሊየን ብር በውጭ ምንዛሪ ሊወጣ የሚችል ገንዘብ መቀነስ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡

የታጁራ የበርበራና የሱዳን ወደቦች ድርሻ እንዲጨምር በመደረጉም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረው አጠቃቀም 7 በመቶ ቀንሷል፡፡

በተጨማሪም ለሞጆ ሁለገብ ሎጂስቲክስ ማዕከል በ11 ሚሊየን ዶላር ወጪ 47 የወደብ ማሽኖች በመገዛታቸው የወደቡን የመጫንና ማራገፍ አቅም መቶ በመቶ ማሳደጉ ተገልጿል፡፡

ከዚያም ባለፈ አማካይ የመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታም ባለፈው ዓመት ከነበረበት 33 ቀናት ወደ 11 ቀናት ዝቅ በማለቱ 491 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ መቀነስ እንደተቻለም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡

ከባቡር አገልግሎት ጋር በተያያዘም ሽፋኑን በማጠናከር በገቢና ወጭ ዕቃ ትራንስፖርት ወጪ ላይ የ860 ነጥብ 31 ሚሊየን ብር ቀንሷል፡፡

በአጠቃላይም በሃገር ውስጥ በተለያዩ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ጉዳዮች በተደረገ ጥረት በድምሩ እስከ 2ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪን ማዳን መቻሉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version