ቢዝነስ

62 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ለገበያ ዝግጁ እየተደረገ ነው

By Alemayehu Geremew

September 07, 2021

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኑሮ ውድነትንና የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቀነስ 62 ሚሊየን ሊትር ጥራቱን የጠበቀ የምግብ ዘይት ለገበያ ዝግጁ መደረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አበባ ታመነ ገለፁ፡፡

የምግብ ዘይት አቅርቦትና ስርጭት መስተጓጎልን ለማስቀረት ብሎም አቅርቦቱን ለማሳደግ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ የገለፁት፡፡

36 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጪ እየገባ ሲሆን ቀሪው 25 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሸፈንም ተገልጿል።

በዛሬው ዕለትም በኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት እና በሌሎች የገባው የምግብ ዘይት ባለ ሁለት፣ ሦሥት እና አምስት ሊትር እንደሆኑና ሃምሳ በመቶውን የሚሸፍነው ባለ አምስት ሊትር የምግብ ዘይት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የገባው ዘይት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በሸማች ማህበራት በኩል በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እና በነገው ዕለት የሚሰራጭ ይሆናልም ነው ያሉት።

በቀጣይነትም በባቡር ስለሚገባ የአቅርቦት ችግር እንደማይኖር ከኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡