የሀገር ውስጥ ዜና

አሸባሪውን ህወሓት ከሰራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ደምስሰነዋል – የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

By Meseret Demissu

September 05, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በማይጠብሪ ግንባር አሸባሪውን ህወሓት ከሰራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ደምስሰነዋል  ሲሉ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ ከአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር የተቀናጀ ጥቃት በመፈፀም አሸባሪው ህወሓት እንዲደመሰስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበራ ጥላሁን እንደገለፁት፥ ነዋሪው ሴት ወንድ ሳይል አሸባሪውን በመዋጋት በጀግንነት ተፋልሟል።

ለአሸባሪው ሃይል በሁሉም አካባቢዎች ማህበረሰቡ ፋታ በመንሳት ከሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ ጭምር በጀግንነት በመዋጋቱ ጁንታው እንዲደመሰስና ቀሪውም እንዲሸሽ አድርጎታል  ብለዋል።

“በቀጣይም በየትኛውም አካባቢ መፈናፈኛ በማሳጣት በመዋጋት ቡድኑን ለማጥፋት ዝግጁ ነን” ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አፀደ አለሙ፥ “ሰራዊታችን በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ከመደገፍ በተጨማሪ አብረን በመሰለፍ የጠላት ህልውና እንዲያበቃ እንደርጋለን” ነው ያሉት ፡፡

ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው አሻባሪ ሃይል ዳግም እንዳይነሳ አከርካሪው መመታት እንዳለበትም ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በማይጠብሪ ግንባር ዳግም እንዳይመለስ የማያደርግ እርምጃ እንደተወሰደበትም ተናግረዋል።

“አገር ለማፍረስ የመጣውን አሸባሪው ዳግም እንዳይነሳ አድርገን እንቀብረዋለን” ብለዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ላይ የህልውና ዘመቻ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ፣ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት ለ24 ሰዓት የከተማቸውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን አቶ እያያው ታደለ የተባሉት የከተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል።

“አሸባሪው ቡድን ግብዓት መሬት እስከ ወዲያኛው እስኪፈጸም ለሰላምና ፀጥታችን ዘብ መሆናችን ይቀጥላል”  ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለያዩ ግንባሮች የሚገኙ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው ሁሉ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ምቶችን መቋቋም ባለመቻሉ በሽሽት ላይ መሆኑንን እየገለጹ ይገኛሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!