አዲስ አበባ ፣ ጥር 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተከናወነ በሚገኘው ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና 27 የተለያዩ የድንበር መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።
በዚህም እስካሁን ለ47 ሺህ 162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በእነዚህ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ 1 ሺህ 695ቱ ተጓዦች ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት የመጡት መሆናቸውን ጠቁሟል።
አሁን ላይ በቫይረሱ የተጠረጠሩ አንድ ቻይናዊ እና ሶስት ኢትዮጵያውያን በድምሩ አራት ሰዎች መለየታቸውን እና፥ አንደኛው በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።
በቫይረሱ በመያዝ ከተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ናሙና ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋልም ነው ያለው።
በተጨማሪም ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሀገር ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ፣ አድራሻ እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝ እስከ 14 ቀን ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ተብሏል።
ይህም ምልክት በሚያሳዩበት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት እንደሚረዳ ነው የተጠቆመው።
ከዚህ ባለፈም ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን ተዋቅሮ ለ24 ሰዓት በፈረቃ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፥ የቫይረሱ ምልክት ጥቆማ በተሰጠ በ2 ሰዓት ውስጥ የማጣራት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ለዚህ ስራ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የታክሲ ማህበራት፣ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች እና የግንባታ ቦታዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በቦሌ ጨፌ ያለው የህክምና ቦታ እና የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለህክምና መስጫነት ተመርጠዋል።
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ማረጋገጫ ምርመራ ሪኤጀንት በዓለም የጤና ድርጅት ትብብር ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚገባ እና ይህም በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎችን በመለየት እና አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ለወረርሽኙ ቁጥጥር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብሏል መግለጫው።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል።
በዚህም ብሔራዊ ግበረ ሀይል እና በኢንስቲቲዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል።
ከዚህ ባለፈም ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።
በተመሳሳይ ዛሬ ለ200 የሚሆኑ የሆስፒታል አመራሮች እና ባለሙያዎች በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።