አዲስ አበባ ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዋትስ አፕ የተሰኘው የፅሁፍ እና የምስል መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ በሚሊየን በሚቆጠሩ ዘመናዊ ስልኮች ላይ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት ሊያቋርጥ መሆኑን አስታወቀ።
ዕቅዱ በተለይም ኦፕሬቲንግ ሲስተማቸውን ማዘመን ባልቻሉ የአንድሮይድ እና አይፎን ስልኮች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ነው የተገለጸው።
እርምጃው የደንበኞችን የመረጃ ደህንነት ለመጠበቅ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ኩባንያው ገልጿል።
በዚህ መሰረት መተግበሪያው አይፎን ኦፕሬቲንግ ሲስተም አይ ኦ ኤስ 8ን ጨምሮ ከዚያ በፊት በተመረቱ ተመሳሳይ መለያ ባላቸው ስልኮች ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት እንደሚያቆም ተገልጿል።
እንዲሁም አንድሮይድ 2፣3፣7 እና ከዚያ በፊት ያሉትን ያልዘመኑ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች የሚጠቀሙ ዘመናዊ ስልኮች ላይ የሚሠጠውን እንደሚያቋርጥም ተነግሯል።
በመተግበሪያው ላይ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፥ ይህም የመረጃ ደህንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ ደንበኞች ሀሰተኛ ገጽ በመክፈት የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን እንዳያሰራጩ የሚያግዝ ነው መሆኑን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!