Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ገለጸ።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ በቻይና የተቀሰቀሰውን የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ተግባር አስመልክቶ  ባወጣው መግለጫ፥ የቻይና መንግስት ቫይረሱ በሀገሪቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የተጠናቀረ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋርም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በቅርበት እየሰራ መሆኑን መግለጫው አክሏል።

ኢትዮጵያን መዳረሻቸው የሚያደርጉ የቻይና ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የሚደረጉ አስፈላጊ ምርመራዎችን አልፈው መሆን እንዳለበት ኤምባሲው አቋሙን ገልጿል።

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱ እየተስፋፋበት ካለው ፍጥነት አንጻር የአለም የጤና ስጋት በመሆኑ አለም ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በሽታውን ለመከላከል የቻይና መንግስት ጥረት እያደረገ ቢሆንም በሽታው የአለም የጤና ስጋት በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻው ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩን ጨምሮ የአለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች ቫይረሱ መጀመሪያ የተቀሰቀሰባትን ውሃን ከተማ መጎብኘታቸውን መግለጫው አውስቷል።

በሽታውን ለመከላከል በቻይና በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ የመከሩ ሲሆን ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቻይና እያደረገች ያለውን ተግባርም አድንቀዋል።

ለአለም የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና በመቆጣጠር የአለምን ህዝብ ደህንነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ተግባር ያስፈልጋል ብለዋል ዶክተር ቴድሮስ።

ቻይና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አቅም እንዳላት ያስቀመጠው የኤምባሲው መግለጫ፤ ለዚህም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳላት ጨምሯል።

በሌላ በኩል ቻይና በሽታውን በተመለከተ በግልጽነትና በሃላፊነት በተሞላው ወቅታዊ መረጃዎችን ለአለም ይፋ የምታደርግ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ከአንድ ወር በፊት በቻይና የውሃን ከተማ የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ እስካሁን ከ300 በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከ14 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

ቫይረሱ ከቻይና ውጪ ወደ ሌሎች የአለም አገሮች እየተስፋፋ ሲሆን ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ሌሎች አገሮች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል።

በሽታው ሲጀምር የትኩሳት ምልክት ሲያሳይ ደረቅ ሳል አስከትሎ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል።

 

 

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

Exit mobile version