አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2020ው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶችና አስልጣኞች በብሔራዊ ቤተመንግሥት ሽልማት ተሰጠ።
የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን የማይመጥን ቢሆንም በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን የሚያመላክት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ29ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያን ለወክሉ እውቅና እና ሽልማት በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።
በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ተካሂዶ በነበረው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ሰሎሞን ባረጋ 40 ግራም ወርቅ እና የ3 ሚሊዮን ብር መኪና ተበርክቶለታል።
በ3000 ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ለሜቻ ግርማ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሽልማት ሲበረከትለት፤ በሴቶች 10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ውድድሮች ለአገራችን የነሐስ ሜዳልያ ላስገኙት አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና ጉዳፍ ፀጋይ እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ 4ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ ዲፕሎማ ላገኙት ሮዛ ደረጀ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ እና መቅደስ አበበ የ200 ሺህ ብር፤ እንዲሁም በተለያዩ ውድድሮች ከ5-8ኛ የወጡ አትሌቶች 150ሺህ ብር ተሸልመዋል።
አትሌቶችን ለውጤት ያበቁ አሰልጣኞችና ምክትሎቻቸዎ እንደየተሳትፏቸው ከ70 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በብሔራዊ ቤተመንግሥት በተካሄደው የዕውቅና እና ሽልማት ስነስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የተለያዩ አመራሮች ተገኝተዋል።
በሱራፌል ደረጄ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!