Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር ችግኝ ለኤርትራ ላከች

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሃገራት ለመስጠት ቃል ከገባችው ችግኝ የመጀመሪያው ዙር ለኤርትራ መላኩን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

በሃገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ሲተገበር ቆይቷል።

የቴክኒክ ኮሚቴው አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የዕቅዱ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የክልሎችን ሪፖርት ጨምሮ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከሌሎች የተሰባሰበው መረጃ ውጤቱ ጥሩ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

በሃገሪቷ አለመረጋጋት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ዕቅዱ በሚፈለገው ልክ አልሄደም ያሉት ዶክተር አደፍርስ፥ ትግራይ፣ አማራና አፋር አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ ትግበራው ወደኋላ እንደቀሩ ጠቁመዋል።

በሌሎች አካባቢዎች ግን በችግኝ ጣቢያዎች የፈሉ ችግኞች በአግባቡ መተከላቸውን ሪፖርቶች አመላክተዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሃገራት ለመስጠት ቃል የገባችው የ1 ቢሊየን ችግኝ ፕሮጀክት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

ሀሳቡን እየተቀበሉ ያሉ ሃገራት መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር አደፍርስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በአምባሳደሮች በኩል ከሃገራቱ ጋር ሰፊ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተወሰኑ ሃገራት የችግኝ ቁጥር ፍላጎታቸውንና የመትከያ ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ ቆንስላዎች በኩል መረጃ እያደረሱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version