አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በፊሊፒንስ ከቻይና ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ተሰምቷል።
በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፈው የ44 ዓመቱ ቻይናዊ ወደ ፊሊፒንስ ከመጓዛቸው በፊት ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀሰቀሰበት ውሃን ከተማ ነዋሪ እንደነበሩ ተገልጿል።
ግለሰቡ ፊሊፒንስ ከመድረሱ በፊት በቫይረሱ ተይዞ የነበረ መሆኑን የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ከግለሰቡ ህልፈት በኋለም ፊሊፒንስ ወደ ቻይና እንዲሁም ከቻይና ወደ ፊሊፒንስ የሚደረግን ማንኛውንም የአውሮፕላን በረራ ሙሉ በሙሉ ሰርዛለች።
አሁን ላይ የዓለም ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ300 በላይ ደርሷል።
በአጠቃላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከ14 ሺህ 300 በላይ ማሻቀቡ ነው የተነገረው።
በቅርቡ በቻይና ውሃን ከተማ የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ወቅት አድማሱን በማስፋት ወደ ተለያዩ ሀገራት እየተዛመተ ይገኛል።
ይህን ተከትሎም አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ከቻይና ወደ ሀገራቱ የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን አግደዋል።