Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ወሰነ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ሥርጭት ለመቀነስ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም መስከረም 1 ቀን 2021 ጀምሮ ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ የሚገደዱትን የመጠባበቂያ መጠን ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑን ብሄራዊ ባንኩ ገልጿል፡፡
እንዲሁም ባንኮች ለአጭር ጊዜ የሚገጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ ወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 ከፍ እንዲል ተደርጓል ሲል መግለጫው አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ አጠቃቀምን በተመለከተ በባንኮች በኩል በሚገኝ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት ችግር ለመግታት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ በአንፃሩ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ አሉታዊ ተፅእኖ እንደማያስከትል ገልጿል፡፡
የውጪ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ አኳያ በትኩረት መሥራት እንደተጠበቀ ሆኖ የተገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ መጠቀም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው ባንኩ ያመለከተው።
የዋጋ ግሽበትን ለመግታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ችግሩን ለመግታት ደግሞ አስፈላጊውን የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ታምኖበታል ብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version