አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በሚቀጥለው ሳምንት ከኢትዮጵያ ይጀምራሉ።
ከፈረንጆቹ የካቲት 6 ጀምረው እስከ የካቲት 14 ቀን 2020 በሚቆየው ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ሴኔጋል ያቀናሉ።
በጉብኝታቸው ውቅትም በየሀገራቱ በሚኖራቸው ቆይታ የኢኮኖሚ እድልና ብልፅግና፣ የዓየር ንብረት ለውጥ፣ ዴሞክራሲ እና የሴቶች እኩልነት ጉዳዮች አብይ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የሀገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያስታወቀው።
በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ይገናኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በዚህም ወቅት በሀገራቱ መካከል ሊኖር በሚችለው የኢንቨስትመንት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ትብብሮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋርም ይወያያሉም ብሏል ፅህፈት ቤቱ።
ኢትዮጵያ እና ካናዳ በአውሮፓውያኑ 1965 ዓመተ ምህርት ይፋዊ ዲፒሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምረዋል።