የሀገር ውስጥ ዜና

በአፋር ክልል ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች ከጎርፍ ስጋት ቀጠና እንዲወጡ ተደረገ

By Alemayehu Geremew

August 28, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል ከ43 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከስጋት ቀጠናው እንዲወጡ መደረጉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን እንደተናገሩት÷ በክልሉ መካከለኛውና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስን ተከትለው የሚገኙ አስር ወረዳዎች በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣሉ።

በዘንድሮ ክረምት ዝናቡ በቀጣዮቹ ሳምንታት እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ የቆቃ፣ ከሰምና ተንዳሆ ግድቦች እየሞሉ የሚመጡበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎች ያመለክታሉ።

“የጎርፍ ውሃ በግድቦቹ ህልውና ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከግድቦች የሚለቀቀውን ውሃ ተከትሎ በወረዳዎቹ የጎርፍ ስጋት ይጨምራል” ብለዋል።

በተለይም በተፋሰሱ ስር የሚገኙ ከ40 በላይ ቀበሌዎች ዋነኛ የጎርፍ ተጠቂዎች ሲሆኑ÷ በእነዚህም ከ95 ሺህ በላይ ሰዎች ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ የዳሰሳ ጥናቶች ማመላከታቸውን አስረድተዋል።

አቶ አይዳሂስ እንዳሉት÷ እስካሁን በአይሳኢታ፣ ገዋኔ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች የክረምቱ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ1 ሺህ 830 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጸው÷ በጎርፍ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡን ከስጋት ቀጠና ለማውጣት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እስካሁን ከጎርፍ ስጋት ቀጠናዎች ያልወጡ ቀሪ ሰዎችም ወቅታዊ የሚቲዎሮሎጂና ተያያዥ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ወደሌላ አካባቢዎች የማስፈሩ ሥራ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

“የእርሻ ሥራ የሚከውኑ ከፊል አርብቶ አደሮች እርሻቸውን ትተው ወደሌላ አካባቢ ለመስፈር አለመፈለጋቸው ሥራው በተፈለገው ደረጃ እንዳይከናወን እንቅፋት ሆኗል” ብለዋል፡፡

ለችግሩ እልባት ለመስጠት በአውሲ-ረሱ እና ገቢ-ረሱ ዞኖች ነዋሪዎችን አሳምኖ ከስጋት ቀጠና ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማስወጣት እየተሰራ ነው ያሉት።

ለእዚህም የማስወጣት ስራውን በቋሚነት ከዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር በመናበብ በቅንጅት የሚያከናውኑ የባለሙያዎች ቡድን ጽህፈት ቤቱ መመደቡን አስረድተዋል።

ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሄዱ የተደረጉ ሰዎች የክረምቱ ዝናብ የመፈናቀል አደጋ እንደደቀነባቸው ተናግረዋል።

ቤተሰቦቻቸውንና እንስሳትን በመያዝ ህይወታቸውን ለማትረፍ ከአካባቢያቸው ወጥተው ወደሌላ የተሻለ ቦታ በጊዜያዊነት መስፈራቸው እንዳለ ሆኖ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል።

የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ ከሚያደርሰውን ጉዳት ለመታደግ መንግስት ጥረት ቢያደርግም ውጤቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

በእዚህም ከፊል አርብቶ አደሮች የሚያለሙት የእርሻ መሬት በጎርፍ እየተጠቃ ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በአዋሽ ወንዝ ሙላት ምክንያት ከ280ሺህ በላይ ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋልጠው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።