Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር ኢትዮጵያ ከገጠሟት ፈተናዎች ለማዳን የሚደረገው ጥረት ለማገዝ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከገጠሟት ፈተናዎች ለማዳን እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማሕበር አባላት ገለጹ።

 

 

 

 

 

ማኅበሩ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

የማኅበሩ የቦርድ አባል ዶክተር ኢዮብ ኃይሌ እንደገለጹት÷ ከምክክሩ ጎን ለጎን በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ለሃገር መከላከያ ሠራዊት 3 ሚሊየን ብር ለመስጠት ቃል ተገብቷል።

ማኅበሩ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የሚገኙ አባላቱ ከመንግስት ጎን በመቆም ሃገር ለማዳን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ከሁሉም በላይ ለሃገር ሠላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል” ያሉት ዶክተር ኢዮብ÷ ኢትዮጵያ ይህን ፈተና በድል ተሻግራ ልማትና እድገቷ ላይ የምታተኩርበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚደረገውን ዘመቻ ለመመከት የዳያስፖራው ተሳትፎ ትልቅ ቦታ እንዳለው በመገንዘብ በዚሁ ላይ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ዳያስፖራው ሃገሩን በተለያዩ መስኮች ለማገዝ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማኅበሩ የቦርድ አባል ሱዓድ ሙክታር ናቸው።

በሀገሪቷ ያጋጠመው የሠላም መደፍረስ ችግር ተወግዶ ሠላም እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ አቋም እንዳለም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የዳያስፖራ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ አሕመድ ሙሕዲን በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ዳያስፖራው በራሱ ተነሳሽነት ውይይቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አሸባሪው ህወሓት ከጋረጠው የሕልውና አደጋ አንፃር ዳያስፖራው ‘ለሀገሬ እቆማለሁ’ በማለት የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም መያዙን ተናግረዋል።

የዳያስፖራ ማኅበሩና አባላቱ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዙ አፍራሽ መረጃዎችን ተከታትሎ የማጋለጥ ስራ እየሰሩ እንደሆነም አክለዋል።

የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር ቀደም ሲል ለመከላከያ ሠራዊቱ የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

         

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version