አዲስ አበባ ፣ ጥር 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በይፋ ተለያየች።
የህብረቱ የ47 አመት የአባልነት ጉዞዋም በፍቺ ሂደቱ ደጋፊዎች የደስታና ፍቺውን በማይደግፉ ብሪታንያውያን ተቃውሞ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በለንደን የብሪ ኤግዚት ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልጹ በአየርላንድ እና ስኮትላንድ ደግሞ ብሪታንያ ከህብረቱ መለየቷን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ተስተውለዋል።
የአውሮፓ ህብረትም የብሪታንያን ከህብረቱ መለየት ተከትሎ የብሪታንያን ሰንደቅ አላማ ብራሰልስ ከሚገኘው የህብረቱ መቀመጫ ቢሮ አውርዶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸውን እና ህዝቡን በአንድነት መንፈስ ወደፊት ለማራመድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ብሪታንያውን ሃገራቸው ከህብረቱ ለመነጠል በምታደርገው ሂደት ላይ የዛሬ ሶስት አመት ነበር ድምጽ የሰጡት።
ከዚያን ጊዜ ወዲህም ብሪታንያ በምትፈጽመው የፍቺ ሂደት እና በሽግግር ጊዜ ከህብረቱ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ መግባባት ለመድረስ ረጅም ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በቅርቡ የደረሱትን ስምምነት ተከትሎም የፍቺ ሂደቱ ሌሊት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ብሪታንያ ከህብረቱ ብትነጠልም እስከ ቀጣዩ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ በሚኖረው የሽግግር ጊዜ ከዚህ ቀደም ይተገበር የነበረውና የሰዎች የመዘዋወር መብትን የማይከለክለው የህብረቱ ህግ ተፈጻሚ ይሆናል።
ከሽግግር ጊዜ በኋላ ከህብረቱ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚወስኑ የንግድ እና መሰል ስምምነቶችንም በቀጣይ እንደምትፈራረም ይጠበቃል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ