የሀገር ውስጥ ዜና

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በደባርቅ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

By Alemayehu Geremew

August 28, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ጃፓን ከሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ጋር በመተባበር በደባርቅ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የንፁሃን ህይወት እንዲያልፍና እንዲፈናቀሉ ማድረጉ ይታወቃል።

ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም÷ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ጃፓን ከሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ጋር በመተባበር ድጋፍ አድርጓል።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅና የድጋፉ አስተባባሪ አስፋው አዛናው እንደገለጹት÷ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ዜጎች 132ሺህ ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ተደርጓል።

የማዕከሉ ሠራተኞችም ለሕልውና ዘመቻው የወር ደመወዛቸውን ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ደብረወርቅ ይግዛው በበኩላቸው÷ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን የከፈተው ጦርነት የንፁሃንን ሞት፣ መፈናቀልና እና የንብረት መውደም አስከትሏል።

ምክትል አስተዳዳሪው ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበው÷ ወራሪው የትህነግ ቡድን በጸጥታ ኀይሉና በኅብረተሰቡ እገዛ እስኪደመሰስ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የደባርቅ ሕዝብ፣ የዞኑ አስተዳደር፣ የተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦችም ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!