Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ63 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ማስፋፊያ ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22 ፣ 2013 (ኤፍር ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከ63 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀው ከፍተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለምረቃ የበቃው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ አንፃርም በእለቱ የተመረቀው ፕሮጀክት ወጣቶችን በሙያና በክህሎት የዳበሩ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ስራ ፈላጊ ወጣቶች አስፈላጊውን ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ እንዲገቡ ኮሌጁ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

የሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሚልኬሳ አህመድ በበኩላቸው ኮሌጁ በርካታ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ስራ እያስገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከጀርመን በተገኘ የ43 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለአውቶሞቲቭ እና ኤሌክትሪካል የስልጠና ትምህርት ክፍሎች አስፈላጊ የሆኑ የስልጠና መሳሪያዎች እንደተሟሉለት ከሃረሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከምረቃ ስነ ስርአቱ በኋላ በሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተከናውኗል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version