የሀገር ውስጥ ዜና

በመተከል ዞን መስከረም ወር ለሚካሄደው ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Tibebu Kebede

August 28, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን መስከረም ወር በመተከል ዞን ለሚካሄደው ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በዞኑ ቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ነው ጄኔራሉ የገለፁት።

በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ከ58 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደየወረዳቸው ማሰባሰብ መቻሉ ምርጫውን በአካባቢያቸው እንዲመርጡ የሚረዳ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ነው ያነሱት።

የፀጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ ለማድረግም በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተመለመሉ ሚሊሻና ምልሶችን አሰልጥኖ በማስታጠቅ የአካባቢያቸውን ፀጥታ እንዲያስከብሩ የማድረጉ ስራ በስኬት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ግቡን ለማሳካት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ልዩ ሀይሎች ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሃያ አራት ሰአት ግዳጃቸውን በጀግንነት እየፈፀሙ ይገኛሉ ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!