Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አምባሳደር ጀማል በከር ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21 2013 (ኤፍ ) በባህሬን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በባህሬን የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ተወካይና የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ከሆኑት አቶ መሀመድ አልዛርካኒ ጋር  ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በትብብርና በቅንጅት አብሮ ለመስራት በሚያስችሉ  ጉዳዮች ዙሪያ  መክረዋል፡፡

በወቅቱም አምባሳደር ጀማል በከር አጠቃላይ ሀገራዊ  ወቅትታዊ ሁኔታ ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የባህሬን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የመካከለኛ ምስራቅ ተወካይ በመሆናቸው፤ በመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለማገዝ እያደረጉ ላሉት እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሰው ሃይል የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ከመነሻ እስከ መዳረሻ ያለውን ሰንሰለት የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ እየተደረገ ያለውን ጅማሮ አድንቀዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ መሀመድ አልዛርካኒ በበኩላቸው፥ የተደረገላቸውን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻና ምስጋና አድንቀዋል፡፡

የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ውስጥ በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የደህንነትና የመብት ጥሰቶችን ለመፍታት በቀጣይ የበለጠ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች በባህሬን ለችግር የሚጋለጡትን ኢትዮጵያን ዜጎች ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱ ኃላፊዎች በቀጣይ በቅርበትና በትብብር አብሮ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version