ዓለምአቀፋዊ ዜና

ለአፍሪካ የተላከው የኮቪድ19 ክትባት በቂ አይደለም – የዓለም ጤና ድርጅት

By Alemayehu Geremew

August 27, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ የተላከው የኮቪድ19 ክትባት በሶስት እጥፍ ቢጨምርም በቂ አለመሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የኮቪድ19 ክትባት የወሰዱት ከሶስት በመቶ በታች የሚሆኑት የአህጉሪቷ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል አመላክቷል፡፡

ማዕከሉ ክትባቱ በፍትሃዊነት አልተከፋፈለም ሲልም ይኮንናል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለአፍሪካ የደረሰው የኮቪድ19 ክትባት በሶስት እጥፍ መጨመሩን የዓለም የጤና ድርጅት የገለፀ ሲሆን÷ 13 ሚሊየን ዶዝ ክትባት እንደተሰራጨም አስታውቋል።

የአሁኑ የክትባት ስርጭት በፈረንጆቹ እስከ መስከረም መጨረሻ 10 በመቶ አፍሪካውያንን ከኮቪድ19 ለመታደግ የተያዘውን ዕቅድ እውን ለማድረግ አዳጋች እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በአህጉሪቷ ካለፈው ሳምንት ወዲህ 248 ሺህ ሰዎች በኮቪድ 19 የተያዙ ሲሆን÷ ቢያንስ በ28 የአፍሪካ ሀገራት የዴልታ ኮቪድ19 ወረርሽኝ መከሰቱን ነው የተመላከተው፡፡

ምንጭ፡-አልጀዚራ