የሀገር ውስጥ ዜና

የህወሓት ተላላኪዎች ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው

By Alemayehu Geremew

August 27, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህወሃት የሚላላኩ የውስጥ ባንዳዎችን ለይቶ በማውጣት አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ገለፀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለምወርቅ ምህረቴ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያካሄዱ እንደሆነም ታውቋል፡፡

የህወሓት የሽብር ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን በፈፀመው ወረራ በርካታ ጥፋቶችን እንዳደረሰ አስተዳዳሪው ጠቁመው፥ ከጦርነቱ የበለጠ የውስጥ ባንዳዎች የሚሰጡት መረጃ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለ ገልፀዋል፡፡

በዘመቻውም የንግዱ ማህበረሰብ ለሰራዊቱ ደጀን በመሆን ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ ሰርጎ ገቦች ላይም እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነና በርካታ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የስብሰባው ተሳታፊዎች አሸባሪውን ህወሓት ለመዋጋት ግንባር ቀደም የነበሩትን የተሳሳተ ስም በመስጠት ትግሉን የሚጎትቱ ባንዳዎች ሊለቀሙ ይገባል ብለዋል።

በዙፋን ካሳሁን እና ምንይችል አዘዘው