የሀገር ውስጥ ዜና

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርና የቃሉ ወረዳ ለመከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን  ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Demissu

August 26, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርና የቃሉ ወረዳ ለመከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገለፁ።

በወሎ ግምባር ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ  ከሀብት ማሰባሰብ ጀምሮ ቆስለው የመጡትን ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር ወደ ቀጠናው ያመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ፥ከኮምቦልቻ ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ዶ/ር ኢንጅነር  ከማል መሐመድ እና ከቃሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ሐሰን እንዲሁም ከአካባቢው አመራሮች ጋር ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያ መክረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ፥ ተግባርን መሰረት ያደረገ አንድነት በመመስረት፣ ህዝባችንን ለማዋረድ የመጣውን ሃይል መመከት የሚያስችል ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን ፕሮፖጋንዳን እንደ አንድ የጦር ስልት እየተጠቀመ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ህብረተሰቡ ለአፍራሽ ፕሮፖጋንዳና የሴራ ፖለቲካ ትንታኔ እንዳይጋለጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ዶ/ር ኢንጅነር  ከማል መሐመድ ለመከላከያ ስራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የውስጥ ተጋላጭነትን ማስወገድና የዘማች ቤተሰቦችን መደግፍ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተማዋ የ24 ሰዓት ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉት ከንቲባው፥ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የመረጃ ጦርነትን ለመፍጠር የሚሞክሩትን መቆጣጠር የሚቻልበትን ስርዓት መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።

የቃሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው ፥በወረዳው ሰርጎ ገቦች ሊገቡባቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

አመራሮቹ በኮምቦልቻ ሆስፒታል በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎችን መጎብኘታቸውን ከኮምቦልቻ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!