Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወላይታ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን የ24 ሰዓት ስርጭት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን የ24 ሰዓት ስርጭት በይፋ መጀመሩ ተገለፀ፡፡

የሥርጭቱ መጀመር የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ ትስስር የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር ለህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሚዲያ ደርሰው ባልተመለከቷቸው የማህበረሰቡን ባህል ወግና እሴት ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ከሙከራ ስርጭት ወደ መደበኛ ስርጭት በይፋ መግባቱ በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንድሚያግዝ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰባ ናና ተናግረዋል።
ይህም ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሥራዎች የጎላ ሚና እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማስተሳሰርና አንድነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት የሚያስችል ቁመና ለመፍጠር ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳደር ዶክተር እንድሪያስ ጌታ በበኩላቸው፥ የወላይታ ብሎም የአጎራባች አካባቢዎች ማህበረሰቡን ዓለም በደረሰበት ለማንቃትና የተጠቃሚዎችን ባህል እሴትና ቋንቋ ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ የደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣናትን የተለያዩ እንግዶችና የሚድያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

በማስተዋል አሰፋ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version