Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሕወሓት ስሙን ከትግራይ ሕዝብ ጋር ቢያቆራኝም የትግራይን ህዝብ አጀንዳው አድርጎት አያውቅም – ዶክተር አብረሃም

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ አሸባሪው ሕወሓት ላለፉት 50 ዓመታት ስሙን ከትግራይ ሕዝብ ጋር አቆራኝቶ ቢጠቀምም አንድም ቀን የትግራይን ህዝብ አጀንዳው አድርጎት እንደማያውቅ ተናገሩ።

ዶክተር አብርሃም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሻባሪው ሕወሓት ሴራና ክፋት ሰለባ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለየ መልኩ ምንም ጥቅም አለማግኘቱ እየታወቀ “በትግራይ ዳያስፖራ በኩል እየተሰራ ያለው ስራ እጅግ ያሳዝናል” ብለዋል ዶክተር አብረሃም።

አንዳንዱ ዳያስፖራ በተሻለ ሃገር የተደላዳለ ኑሮ እየመራ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ ማብቂያ እንዳይኖረው የሽብር ቡድኑን እያገዘ ነው ያሉት ዶክተር አብረሃም፥ “ህዝብ በየደቂቃው እያለቀና ሕጻናት እየረገፉ ምንም የማይመስላቸው የትግራይ ተወላጆች እጅግ የሚያሳዝን ተግባር እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።

ይህም ውክል ናቸው ለትግራይ ሕዝብ ሳይሆን ለአሸባሪው ሕወሓት መሆኑን በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የገለጹት።

አሸባሪው ሕወሓት “በሴራና በአፈና” ሕዝቡን ሲያስተዳድር መቆየቱን ያስታውሱት ዶክተር አብረሃም፥ አሁንም የትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት አማራጭ መረጃ እንዳያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።

በቅድሚያ የትግራይ ሕዝብ ስለ አሸባሪው ሕወሓት የተንኮል ገመና በግልፅ እንዲረዳ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ከራሱ ላይ ነቅሎ ለመጣል ወደ ኋላ የማይል ሕዝብ እንደሆነ በተግባር የተረጋገጠ ነው በማለት ያስረዳሉ ዶክተር አብረሃም።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢሆን “የትግራይን ሕዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር አያይዞ ሊመለከተው አይገባምም” ይላሉ።

የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ የሚኮራ፣ በሃገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

ምንም እንኳን አሸባሪው ሕዝቡን መከታ ለማድረግ ቢንቀሳቀስም የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥፊዎችን ከሰላማዊ ዜጎች መለየት መቻል እንዳለበትም ተናግረዋል።

”በተለያየ መልኩ በሽብር ቡድኑ ኔት ወርክ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ካሉ እነሱን ማጋለጥ ያስፈልጋል ከሃዲ የትም ሊገኝ ስለሚችል” ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ የሚያልፍ በመሆኑ ሕዝብን እንደ ጥፋተኛ መቁጠር ሳይሆን ቀርቦ ማገዝ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ዶክተር አብረሃም አክለውም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ቢሆን “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመቀበል ይልቅ ድብቅ ፍላጎቱን ለማሟላት እየሰራ ይገኛል” ብለዋል በቆይታቸው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version