Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፌዴራልና ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የ13ኛው የፌዴራልና ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጉባዔው “በለውጥ መርህ በተቃኘ አስተሳሰብ የህግ ታራሚዎችን የሰብአዊ መብት አያያዝና የማረም ማነጽ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ እናደርሳለን!” በሚል መሪ ቃል ነው በባቱ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዳመነ ዳሮታ ፣የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሎች ተገኝተዋል።
ጄነራል ዳመነ ዳሮታ በመክፈቻው ላይ ÷ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርዓት መገንባት ከተጀመረ ወዲህ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ዜጎች ወደ ማረሚያ ቤት የማይላኩበት ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል፡፡
ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚላኩ ዜጎች ሠብአዊና ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው ተጠብቆ ይያዛሉ ያሉት ኮሚሽነሩ÷ በቆይታቸውም የቀለም ትምህርትና የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማረሚያ ቤቶች ዜጎች የሚታፈኑበት፣ ግፍና ሰቆቃ የሚደርስባቸው ቦታዎች ሳይሆኑ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ባስቀመጠው መሠረት ታርመውና ታንፀው፣ አምራችና ህግ አክባሪ ሆነው ወደ ሠላማዊ ህይወት የሚመለሱባቸው ተቋማት ሆነዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ከቦታ ቦታ ልዩነት ቢኖርም እንኳን በሁሉም ማረሚያ ቤቶች አበረታች ለውጦችና መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዮስ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የፍትህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በሪፎርም ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ከመጣባቸው ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በሀገራችን በፍትህ ዘርፉ የተቀጣጠለውን የለውጥ መንፈስ ተከትሎ የሀገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ዜጎች ወደ ማረሚያ ቤት የማይላኩበት ስርዓት ተዘርግቷል ሲሉ ገልጸዋልም፡፡
ማረሚያ ቤቶች አሁን ከሚገኙበት ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ግን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ተግባር ነውም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አንጻር የዚህ ጉባዔ ተሳታፊዎች በማረሚያ ቤቶቻችን የሚከናወኑ የተሃድሶ ስራዎች፣ የታራሚዎችን የሥራ ባህል የሚያሳድጉ፤ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የቀለም ትምህርት የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡
ተቋሙ የማረምና ማነፅ ስራውን ከተጨባጭ ወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ እንዲሁም ከዘመናዊ የማረሚያ ቤት የአሠራር ስርዓቶች፣ ቴክኖሎጂዎችና መሠረተ-ልማቶች (ኢንዱስትሪዎች) ጋር እያጣጣመና እያዘመነ መሄድ ይገባዋል፡፡
ዶክተር ጢሞቲዮስ አያይዘውም በዚህ ረገድ አሁን የምንገኝበትን ደረጃ በመፈተሽ የወደፊት የጥበቃና ደህንነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የተሃድሶ ስራ እና የማረምና ማነፅ ስርዓታችን ለማሻሻል የተጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክራችሁ ልትሰሩ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡
በዓመት ሁለት ግዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በጉባኤውም የ12ኛው ጉባዔ ቃለ ጉባኤ መርምሮ ማጽደቅ፣ የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ተቋማት ሪፎርም አፈጻጸም የሚገኝበት ደረጃ መገምገም ፣ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት መሆኑ ተገልጿል ፡፡
በተጨማሪም በሃገራዊ ማረሚያ ቤቶች ፀጥታና ደህንነትና ሌሎች ተጨማሪ አጭር መነሻ እቅድ ቀርቦ ዉይይት ተካሄዶበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
በመሰረት አወቀ እና መሰረት ደምሱ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version