የሀገር ውስጥ ዜና

ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች ለወጣቶች የህይወት ልምዶቻቸውን አጋሩ

By Meseret Demissu

August 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች ለወጣቶች የህይወት ልምዶቻቸውን አጋርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አዘጋጅነት “የህይወት ልምዴን አካፍላለሁ!” በሚል መሪ ሃሳብ በተሰናዳው የልምድ ልውውጥ  መድረክ ላይ የፌዴራልና የአዲስ አበባ አስተዳደር የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተው ልምዶቻቸውን እያካፈሉ ነው።

በዚሁ መድረክ ላይ የህይወት ተሞክሯቸውን ያቀረቡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማህበራዊ ጉዳዮች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት ማንኛውንም አይነት ፈተና በትግስትና በብልሃት ማለፍ ከተቻላ ያሰቡት ቦታ መድረስ ይቻላል።

እርሳቸው በተማሪነት ዘመናቸው ለሶስት ቀናት ምግብ ሳያገኙ ያሳለፉትን አጋጣሚ አጋርተዋል።

ልጅነታቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደነበር የገለፁት አቶ ጃንጥራር፤ ዛሬ የደረሱበት ስፍራ ለመድረስ ብዙ የህይወት ውጣውረዶችን ማሳለፋቸውን አብራርተዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚማሩት ወቅት በወር 30 ብር እየተላከላቸው ይማሩ እንደነበርና በዛው ወቅትም በነገሮች አለመመቻቸት ምክንያት ለሶስት ቀናት ያለበቂ ምግብ ማሳለፋቸውን ጠቁመዋል።

ምክንያታዊ መሆንና ስኬትን አለማራገብ የህይወት መርሆቻቸው እንደሆኑም አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል፥ ይሄም ለወጣቶች መልካም መሆኑን ገልፀዋል።

የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋም በተመሳሳይ የህይወት ልምዳቸውን ለወጣቶቹ ማጋራታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!