Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ቻይና እንደምትደግፍ አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ቻይና እንደምትደግፍ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያን ዪ አስታወቁ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያንይ ዪ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅት በሃገራቱ የሁለትዮሽና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክክር አድርገዋል።

በዚህ ወቅትም የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያን ዪ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት አጥብቃ ትደግፋለች ብለዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳዮቹን በአግባቡ መያዝ የሚችልበት አቅም አለው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ቤጂንግም ኢትዮጵያ ሰላምን በማስፈን መረጋጋት፣ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የምታደረገውን ጥረት ትደግፋለችም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ከዚህ ባለፈም ሃገራቸው በሰብአዊ መብት ሽፋን የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወምም አስረድተዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም በመድረስ ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን መንግስት አቋም እንደሚደግፍ ቻይና እምነቷ መሆኑንም አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፉ መድረክ የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ቻይና ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት በምታደርገው ጥረት ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያም የኢትዮ ቻይናን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂክ የትብብር አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያም እንደ ቻይና ምዕራባውያን በሰብአዊ መብት ስም በሌሎች ሃገራት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት አጥብቃ እንደምታቀወም ጠቅሰዋል።

ምዕራባውያን የኮቪድ19 መነሻን ለማወቅ የሚያደርጉት ጥረትም ከፖለቲካዊ ይዘት በፀዳ መልኩ ሊታይ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version