የሀገር ውስጥ ዜና

በደባርቅ ከተማ 124 ተጠሪጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Meseret Awoke

August 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በተደረገ ክትትል 124 ተጠሪጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የደባርቅ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌትነት ፀጋዬ እንዳሉት÷ አሸባሪው ህወሓት ወደ ከተማዋ ሰርጎ እንዳይገባ ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ ተከናውኗል።

በተለይም ህብረተሰቡን በየመንደሩ የማደራጀት፣ ስለወቅታዊ ሁኔታ ግልፅ ግንዛቤ የመፍጠር እና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ተመልምለው መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና በመስጠት የማደራጀት ተግባር መከናወኑን ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቁ በኬላዎች እና በመንደር ውስጥ ፍተሻ እንዲያደርጉ ሃላፊነት እንደተጣለባቸውም አብራርተዋል።

በኬላዎች እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተደረገ ክትትል 124 ተጠሪጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ጌትነት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በምሽት የኬላ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት አቶ በላይ አማረ እና አቶ ምህረት መንግስቱ እንደተናገሩት÷ አሸባሪው ህወሓት በከተማዋ ሰርጎ በመግባት ጥቃት እንዳያደርስ እየተከታተሉ ነው።

አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በመግባት ጥቃት እንዳይፈፅም “ሁሉም በያለበት አካባቢውን መጠበቅ አለበት” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!