Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህወሓትን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን-የኢፌዴሪ አየር ሃይል

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓትን “በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን” ሲል የኢፌዴሪ አየር ሃይል ገለጸ።
 
የኢፌዴሪ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ÷አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየበት ወቅት አየር ሀይልን በትኖ እና ዘርፎ ወደ መቀሌ መሸሹን ተናግረዋል።
 
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ በተቋሙ በተሰራው የሪፎርም ስራ አየር ሃይሉ በሙሉ ቁመናና ዝግጁነት ላይ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉን አብርራተዋል።
 
በዚህ ምክንያትም አሸባሪው ህወሓት አየር ሃይልን በትኖ እና ዘርፎ መሄዱን አስታውሰው÷አየር ሃይሉ እርሱ ባስቀመጠበት ቦታ ያለ መስሎት በመጀመሪያው የህልውና ዘመቻ ወቅት ጦርነት መክፈቱን ነው የተናገሩት።
 
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በማድረግ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ አሸባሪው ቡድን በአጎራባች የሚገኙ የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አንስተዋል።
 
ይህ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ የተለያዩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
 
ይሁን እንጂ የዚህ የሽብር ቡድኑ ዓላማ በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትና አገር ወዳድ ዜጎች የጋራ ትብብር እየከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ደጀን ህዝባችንን ይዘን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በመቋጨት “አሸባሪውን ህወሓት በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማቱ እናዞራለን” ነው ያሉት።
 
ኢትዮጵያ በየትኛውም የጥፋት ሃይል የማትፈርስ ታላቅ አገር መሆኗን የተናገሩት ኮሎኔል ተሾመ ÷ በቡድኑ ላይ በጋራ ክንድ ድል እናረጋግጣለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version