Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህብረተሰቡ አሸባሪዎች የሀገርን አንድነት ለመናድ ከሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ ራሱን መጠበቅ አለበት- ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪውዎቹ ህወሓትና ሽኔ የሀገርና የህዝብ አንድነትን ለመናድ ከሚያሰራጩት የሐሰት ወሬ ህብረተሰቡ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ምሁራን አሳሰቡ፡፡
 
ምሁራኑ “ህወሓትና ሸኔ በጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ መስማማታቸው ሽብርተኝነታቸውን እንደገፉበት ማሳያ ነው” ብለዋል።
 
በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ሁሴን የሱፍ÷ የኢትዮጵያን እድገት መሰረት የሚስይዙ የህዳሴው ግድብን ጨምሮ በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው እረፍት የነሳቸው የሀገር ጠላቶች ከውስጥና ከውጭ ተደራጅተው እያጠቁን ነው።
ሕወሓትና ሸኔ በሀሰት ወሬ የሀገሪቱን ገፅታ ለማበላሸትና የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የጀመሩትን ጦርነት ሁሉም የኢትዮጵያዊ በአንድነት ማውገዝና ማጋለጥ አለበት ብለዋል፡፡
 
አሸባሪው ህወሀትና ተላላኪው የሸኔ ቡድን የሀገርና የህዝብን አንድነት ለመናድ ከሚያሰራጯቸው የሀሰት ወሬዎች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 
አንዳንድ የውጭ መንግስታትም ቢሆኑ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም ሲሉ ለአሸባሪ ቡድኖቹ ድጋፍ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ወጣቱ ሀገር ለማፍረስ የተነሱ የአሸባሪ ቡድኖችን ሴራ በመገንዘብ ራሱን በመጠበቅና ተባባሪና ወሬ አቀባዮችን በማጋለጥ ሀሩን ከጥፋት ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
“ኢትዮጵያ አንድ የሚያደርጋት መንግስት እንጂ በውሸት መሰረት ላይ ተዋቅሮ የሀገር አንድነት ለመበተን የሚመጣ ቡድን አያስፈልጋትም” ያሉት አቶ ሁሴን “ኢትዮጵያውያን መጨረሻችን የእነ የመንና ሊቢያ እጣ እንዳይሆን ከውሸት መረጃ መጠበቅ ይኖርብናል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
 
“የህወሓት ቡድን ቀድሞ በዘረፈው ገንዘብ በውጭ የብዙሀን መገናኛዎች የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፉ መረጃዎችን የሚያሰራጭበት ትልቁ አላማ ህዝብን እያወናበደና ሀገር እየዘረፈ የመኖር ምኞቱን ለማሳካት የያዘውን አጀንዳ ለማስፋፋት ነው” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አሚን መሀመድ ናቸው፡፡
ዶክተር አሚን አክለውም ህወሓትና ሸኔ በጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ መስማማታቸው ሽብርተኝነታቸውን ያጠናከሩበት ስለመሆኑ ማሳያ ነው” ማለታቸውን ኢዜ ዘግቧል፡፡
“ቡድኖቹ በሚያሰራጩት የውሸት ፕሮፓጋንዳ የብዙዎች ወጣቶች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኖ ኖሯል” ያሉት ዶክተር አሚን÷ ወጣቶች የሃሰት መረጃዎችን በመቀባበል ወዳልተገባ መንገድ ከመሄድ እንዲጠነቀቁ መክረዋል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version