Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፋር ሕዝብ ራሱን ወደ ሽፍትነት የለወጠውን አሸባሪውን ህወሃት መድረሻ ሊያሳጣው ይገባል-አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ሕዝብ ራሱን ወደ ሽፍትነት የለወጠውን አሸባሪውን ህወሃት መድረሻ እንዲያሳጣው የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰመራ ለከተማ ከአርቲስቶች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በወቅቱ እንደገለጹት የክልሉ ሕዝብ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ የደረሰበት የህወሀት ቡድን ተስፋ ቆርጦ ወደ ተራ ሽፍትነት ስለተቀየረ ተከታትሎ ሊደመስሰው ይገባል።
“ቡድኑ በእብሪት የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ በክልሉ ልዩ ሃይልና መከላከያ ሠራዊት በተወሰደ እርምጃ ተመትቶ መውጫ ጠፍቶበት እየተርመጠመጠ ይገኛል” ያሉት ርእሰ መሰተዳደሩ ሕዝቡ በየስርቻው የገባውን ጠላት በመደምሰስ ራሱንና አካባቢውን እንዲያጸዳ አሳስበዋል።
ህወሃት ክልሉን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን የማፍረሱ ሴራ እንዳልተሳካ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገር በማዳን ዘመቻው የተመዘገቡ አኩሪ ገድሎችና ታሪክ ትውልድን እንደሚያኮሩ ገልጸዋል።
የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ለማስፈጸም የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሕዝቡንና የጸጥታ ሃይሉን በማነቃቃት ሚናቸውን እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
 
ከተሳታፊ አርቲስቶች መካከል ድምጻዊ አብደላ ያዩ በሙያው ሰራዊቱንና ህብረተሰቡን በማዝናናትና በማነቃነቅ ሀገሪቱን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል።
 
ሌላዋ የሙዚቃ ባለሙያ ሐዋ መሐመድ በበኩሏ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ጥበቃና ድጋፍ የምትፈልግበት ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆኗን ገልጻ ሙያና ሀገራዊ ግዴታዋን ለመወጣት እንደተዘጋጀች ተናግራለች።
በውይይቱ ላይ ሙዚቀኞች፣ የግጥምና የሥነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version